Ezekiel 39

1“አንተ የሰው ልጅ ሆይ፤ በጎግ ላይ ትንቢት ተናገር፤ እንዲህም በል፤ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “የሞሳሕና የቶቤል ዋና አለቃ
ወይም የሮሽ አለቃ ጎግ
ጎግ ሆይ፤ ተነሥቼብሃለሁ፤
2ወደ ኋላ እመልስሃለሁ፤ እንዲሁም እጐትትሃለሁ፤ ከሩቅ ሰሜን አምጥቼ በእስራኤል ተራሮች ላይ እሰድድሃለሁ። 3በግራ እጅህ ያለውን ቀስትህን እመታለሁ፤ በቀኝ እጅህ የያዝሃቸውንም ፍላጾች አስረግፍሃለሁ። 4አንተና ወታደሮችህ ሁሉ፣ ከአንተም ጋር ያሉ ሕዝቦች በእስራኤል ተራሮች ላይ ትወድቃላችሁ። ነጣቂ አሞሮችና የዱር አራዊት ይበሏችሁ ዘንድ አሳልፌ እሰጣችኋለሁ። 5አውላላ ሜዳ ላይ ትወድቃለህ፤ እኔ ተናግሬአለሁና፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር 6በማጎግና ያለ ሥጋት በባሕር ዳርቻ በሚኖሩት ላይ እሳት እሰድዳለሁ፤ እነርሱም እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።”

7“ ‘ቅዱሱ ስሜ በሕዝቤ በእስራኤል ዘንድ እንዲታወቅ አደርጋለሁ፤ ከእንግዲህ ወዲያ ቅዱስ ስሜ እንዲናቅ፣ እንዲቃለል አልፈልግም፤ አሕዛብም እኔ እግዚአብሔር የእስራኤል ቅዱስ እንደ ሆንሁ ያውቃሉ። 8እነሆ ይመጣል፤ በርግጥም ይሆናል፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ ያ ያልሁት ቀን ይህ ነው።

9“ ‘ከዚያም በእስራኤል ከተሞች የሚኖሩ ሁሉ ወጥተው የጦር መሣሪያውን፣ ትልልቁንና ትንንሹን ጋሻ፣ ቀስቱን፣ ፍላጻውን፣ የጦር ዱላውንና ጦሩን ሰብስበው ማገዶ በማድረግ ያነድዱታል፤ ሰባት ዓመት ይማግዱታል። 10ከሜዳ ላይ ዕንጨት መልቀም፣ ከዱርም ዛፍ መቍረጥ አያስፈልጋቸውም፤ የጦር መሣሪያቸውን በመማገድ ይጠቀማሉና። የዘረፏቸውን ይዘርፋሉ፤ የበዘበዟቸውን ይበዘብዛሉ፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር

11“ ‘በዚያ ቀን ሰዎች በምሥራቅ በኩል ወደ ባሕሩ
ሙት ባሕርን ያመለክታል።
በሚጓዙበት ሸለቆ፣ ለጎግ የመቃብር ስፍራ በእስራኤል እሰጠዋለሁ። ጎግና ሰራዊቱ ሁሉ በዚያ ስለሚቀበሩ፣ የተጓዦችን መንገድ ይዘጋሉ፤ ስለዚህም የሐሞን ጎግ
ሐሞን ጎግ ማለት የጎግ መንጋ ማለት ነው።
ሸለቆ ይባላል።

12“ ‘ምድሪቱን ለማጽዳት፣ የእስራኤል ቤት ሰዎች ሰባት ወር ሙሉ ይቀብሯቸዋል። 13የምድሪቱ ሰዎች ሁሉ ይቀብሯቸዋል፤ እኔ የምከብርበትም ዕለት የመታሰቢያ ቀን ይሆናቸዋል፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር

14“ ‘ሰዎች ምድሪቱን ለማጽዳት በየጊዜው ይቀጠራሉ። አንዳንዶቹ ምድሪቱን ያሥሣሉ፤ ከእነርሱም በተጨማሪ ሌሎች ሳይቀበሩ የቀሩትን ይቀብራሉ። ከሰባት ወር በኋላም ፍለጋ ይጀምራሉ። 15እነርሱም በምድሪቱ መካከል ሲሄዱ፣ ከእነርሱ አንዱ የሰው ዐፅም ባየ ቍጥር ምልክት ያደርግበታል፤ ይህም መቃብር ቈፋሪዎች በሐሞን ጎግ ሸለቆ እስኪቀብሩት ድረስ ነው። 16በዚያም ሐሞና
ሐሞና ማለት መንጋ ማለት ነው።
የምትባል ከተማ አለች፤ ስለዚህ ምድሯን ያጸዳሉ።’

17“የሰው ልጅ ሆይ፤ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘ማንኛውንም ዐይነት ወፍና የዱር አራዊት ሁሉ ጥራ፤ እንዲህም በላቸው፤ ከየአቅጣጫው ተሰብስባችሁ እኔ ወደማዘጋጅላችሁ መሥዋዕት ኑ፤ ይህም በእስራኤል ተራሮች ላይ የሚሆን ታላቁ መሥዋዕት ነው። በዚያ ሥጋ ትበላላችሁ፤ ደምም ትጠጣላችሁ። 18እንደ አውራ በግና እንደ ጠቦት፤ እንደ ፍየልና እንደ ወይፈን፣ የኀያላን ሰዎችን ሥጋ ትበላላችሁ፤ የምድርንም መሳፍንት ደም ትጠጣላችሁ፤ እነዚህ ሁሉ የሰቡ የባሳን ከብቶች ናቸው። 19እኔ በማዘጋጅላችሁም መሥዋዕት እስክትጠግቡ ሥብ ትበላላችሁ፤ እስክትሰክሩም ደም ትጠጣላችሁ። 20በገበታዬም ፈረሶችንና ፈረሰኞችን፣ ኀያላን ሰዎችንና ከየወገኑ የሆኑትን ወታደሮች እስክትጠግቡ ትበላላችሁ፤’ ይላል ጌታ እግዚአብሔር

21“ክብሬን በአሕዛብ መካከል እገልጣለሁ፤ አሕዛብም ሁሉ በእነርሱ ላይ ያመጣሁትን ቅጣትና በላያቸው ላይ የጫንሁትን እጅ ያያሉ። 22ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የእስራኤል ቤት እኔ እግዚአብሔር፣ አምላካቸው እንደ ሆንሁ ያውቃሉ። 23አሕዛብም የእስራኤል ሕዝብ ለእኔ ታማኞች ባለመሆን ከሠሩት ኀጢአት የተነሣ እንደ ተሰደዱ ያውቃሉ፤ ስለዚህ ፊቴን ከእነርሱ ሰወርሁ፤ ለጠላቶቻቸው አሳልፌ ሰጠኋቸው፤ ሁሉም በሰይፍ ወደቁ። 24እንደ ርኩሰታቸውና እንደ በደላቸው መጠን ፈረድሁባቸው፤ ፊቴንም ከእነርሱ ሰወርሁ።

25“ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ያዕቆብን አሁን ከስደት እመልሰዋለሁ፤
ወይም አሁን የያዕቆብን ዕድል አድሳለሁ
ለእስራኤል ሕዝብ ሁሉ እራራለሁ፤ ስለ ቅዱስ ስሜም እቀናለሁ።
26የሚያስፈራቸው ማንም ሳይኖር በምድራቸው በሰላም በሚኖሩበት ጊዜ፣ ውርደታቸውንና ለእኔ ታማኝ ሆነው ያልኖሩበትን ዘመን ይረሳሉ። 27ከአሕዛብ ምድር መልሼ ሳመጣቸው፣ ከጠላቶቻቸው አገር ስሰበስባቸው የራሴን ቅድስና በእነርሱ በኩል በብዙ ሕዝቦች ፊት አሳያለሁ። 28በአሕዛብ መካከል እንዲሰደዱ ባደርግም፣ አንድም ሳላስቀር ወደ ገዛ ምድራቸው እመልሳቸዋለሁ፤ ከዚያም እኔ እግዚአብሔር አምላካቸው እንደ ሆንሁ ያውቃሉ። 29ከእንግዲህ ፊቴን ከእነርሱ አልሰውርም፤ መንፈሴን በእስራኤል ቤት ላይ አፈስሳለሁና፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።”

Copyright information for AmhNASV